Psalms 28

ልመናና ምስጋና

የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤
ዐለቴ ሆይ፤ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሁንብኝ፤
አንተ ዝም ካልኸኝ፤
ወደ ጕድጓድ እንደሚወርዱ እሆናለሁ።
2ለርዳታ በጮኽሁ ጊዜ፣
ወደ ቅዱስ ማደሪያህ፣
እጆቼን በዘረጋሁ ጊዜ፣
የልመናዬን ቃል ስማ።

3በልባቸው ተንኰል እያለ፣
ከባልንጀሮቻቸው ጋር በሰላም ከሚናገሩ፣
ከክፉ አድራጊዎችና
ከዐመፃ ሰዎች ጋር ጐትተህ አትውሰደኝ።
4እንደ ሥራቸው፣
እንደ ክፉ ተግባራቸው ክፈላቸው፤
እንደ እጃቸው ሥራ ስጣቸው፤
አጸፋውን መልስላቸው።

5 ለእግዚአብሔር ሥራ ግድ ስለሌላቸው፣
ለእጆቹም ተግባራት ስፍራ ስላልሰጡ፣
እርሱ ያፈርሳቸዋል፤
መልሶም አይገነባቸውም።

6የልመናዬን ቃል ሰምቷልና፣
እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን።
7 እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤
ልቤ በእርሱ ይታመናል፤ እርሱም ዐግዞኛል፤
ልቤ ሐሤት አደረገ፤
በዝማሬም አመሰግነዋለሁ።

8 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ብርታታቸው ነው፤
ለቀባውም የመዳን ዐምባ ነው።
9ሕዝብህን አድን፤ ርስትህንም ባርክ፤
እረኛ ሁናቸው፤ ለዘላለሙም ዐቅፈህ ያዛቸው።
Copyright information for AmhNASV